ኒውክሊየር ኃይል ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?


የኒውክሊየር ኃይል አስተማማኝና የማይለዋወጥ የኃይል ምንጭ በመሆኑ
የኒውክሊየር ኃይል አስተማማኝ፣ የማይለዋወጥና ለመሠረታዊ የኃይል ፍላጎት (Baseload) ተስማሚ የኤሌክትሪክ ምንጭ ነው። የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫዎች በአየር ሁኔታ ላይ ጥገኛ አይደሉም፤ ስለሆነም በቀንና በሌሊት በተከታታይ ሊሠሩ ይችላሉ። በተለምዶ እስከ 18 ወራት ያህል ያለማቋረጥ ከሠሩ በኋላ ለየት ላለ ጥገናና ለነዳጅ መሙላት ይቆማሉ።
ኒውክሊየር ኃይልን ወደ የኢትዮጵያ የኃይል አማራጭ (Energy Mix) ማካተት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማረጋጋት እና በረጅም ጊዜ ተጠቃሚዎች ለኤሌክትሪክ የሚያወጡትን ዋጋ ለመቀነስ ሊያግዝ ይችላል።

ንጹህና ለአካባቢ ተስማሚ በመሆኑ
በኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ውስጥ ኤሌክትሪክ በሚመነጭበት ወቅት ካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO₂) ወደ ግሪን ሀውስ ጋዝ በቀጥታ አይለቀቅም። ስለዚህ ኒዩክሊየር ኃይል የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና የንጹህ ኃይል ሽግግርን ለመደገፍ ጠቃሚ ሚና ይኖረዋል።

በረጅም ጊዜ ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ
የኒውክሊየር ኃይል ለረጅም ጊዜ ሊያገለግል የሚችል የተረጋገጠ የቴክኖሎጂ አማራጭ ሲሆን፣ የዩራኒየም ነዳጅን ይጠቀማል። የኒውክሊየር ማመንጫዎች የረጅም የሥራ ዕድሜ፣ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት እና ከነዳጅ አጠቃቀም አንጻር ከፍተኛ የኃይል ውጤታማነት ያላቸው በመሆናቸው፣ በረጅም ጊዜ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ወጪን በተመጣጣኝ ደረጃ ለማስቀመጥ ሊያግዙ ይችላሉ። ዘመናዊ የኒውክሊየር ማመንጫዎች የአገልግሎት ዕድሜያቸው እስከ 60 ዓመት ሊደርስ የሚችል ሲሆን፣ በተጨማሪም ለ20 ዓመታት ሁለት ጊዜ ሊራዘም ይችላል።

ለኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ዕድገት ያለው ሚና
የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ በአገልግሎትና በአቅርቦት ሰንሰለት በኩል ለሀገራዊና ለአካባቢያዊ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል። በማመንጫው ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችና ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራና የንግድ ዕድሎች በመፍጠር ኢኮኖሚን ያነቃቃል።
አስተማማኝና በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መኖሩም ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብና የኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን የሚያግዝ መሠረተ ልማት ይሆናል።

ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው ሚና
የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ በግንባታ ወቅት ብዙ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል፤ ይህም ከማመንጫው ግንባታ ጀምሮ በኋላም ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የሙያ ዕድሎችን ይፈጥራል። በተለይም በኢንጂነሪንግ፣ በኒውክሊየር ሳይንስ፣ በአይቲ፣ በኮንስትራክሽን ፣ በጥገና፣ በደህንነትና በማኔጅመንት ዘርፎች ከፍተኛ የእውቀትና የክህሎት የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ።
በመሆኑም የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም ከግንባታ እስከ ሥራ ማስኬድና ጥገና ድረስ በርካታ የሰው ኃይል ልማትና የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ለኢትዮጵያ የእውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
