ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 የአፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉበት የኒውክሊየር ኃይል የፋይናንስ ማዕቀፎች አቅምን ለማጎልበት ያለመ ስልጠና በይፋ ተጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይልን ለማልማት በሚያስፈልጉ የፋይናንስ ማዕቀፎችና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ላይ ያተኮረ ክልላዊ ስልጠና ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ማካሄድ ጀምራለች ።
የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ስልጠና፣ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ-ግብር ለመጀመር በዝግጅት ላይ ላሉ ሀገራት የፋይናንስ ማዕቀፎችን ለመረዳትና ተግባራዊ አቅምን ለማጎልበት ያለመ ነው።
የኒውክሊየር ኃይል መርሃ-ግብርን ለማቋቋም ከፍተኛ የመነሻ ካፒታል፣ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ እቅድና የተለያዩ የገንዘብ ምንጮችን ማስተባበር የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ የፋይናንስ ማዕቀፎችን በትክክል መንደፍ ለመርሃ-ግብሩ ስኬታማነት ወሳኝ ነው።
ከ22 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 39 ተወካዮችን ያሰባሰበው ይህ አውደ ጥናት በአህጉሪቱ ንጹህ እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት እንዲሁም ዘላቂ የኃይል ልማትን ለማፋጠን የተደረገ ትልቅ እርምጃ ነው። ስልጠናው “ለኒውክሊየር ኃይል መርሃ-ግብሮች ጀማሪ ሀገራት የፋይናንስ ማዕቀፎች” በሚል ርዕስ እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።




በኢትዮጵያ በሚገነባው የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ
የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽነር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በሀገሪቱ ሊገነባ የታቀደውን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በሚያስችሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ዝግጅትና በቀጣይ የትግበራ አቅጣጫዎች ላይ ምክክር አድርገዋል።
በዚህም ፕሮጀክቱን በብቃት ወደ መሬት ለማውረድ የሚረዱ ሀገራዊ ቅንጅቶችን አጠናክሮ መቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይህ መድረክ የሀገሪቱን የኢነርጂ ዋስትና ማረጋገጥና በዘርፉ ሀገራዊ አቅም መገንባት የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን በበለጠ ለማፋጠን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለታዳሽና አስተማማኝ የንጹህ ኃይል ልማት ያላት ጽኑ ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መምጣቱን የሚያሳይ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ተገልጿል።


ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሰየሙ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 7ኛው ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመንግሥት መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።
በዚህ የ7ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጉባኤ የመንግሥት መመሥረቻ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ትልቅ ሀገር! ትልቅ ሕዝብ! ታላቅ ርዕይ
እንኳን ደስ አለን!
ኢ.ኒ.ኮ.ኃ
“ኢሬቻ፡ ለሀገራዊ መግባባት!“
Baga Ayyaana Irreechaa bara 2019 nagaan geessan!
“Irreecha: Waliigaltee biyyaalessaaf!“
እንኳን ለ 2019 ዓ.ም ኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
“ኢሬቻ፡ ለሀገራዊ መግባባት!“
Happy 2019 Irreechaa Holiday!
“Irrechaa: for National Consensus!’’


Ethiopian Nuclear Energy Commission
ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ ከመሰከረም 14 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ አብርሃም በላይን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርገው ሾመዋል።
#PMOEthiopia

የኑውክሊየር ኃይል እውነታዎች
የኒውክሊየር ኃይል በአካባቢያችን ያሉ ነገሮች ከሚሰሩበት ከጥቃቅን አተሞች እንደሚገኝ ያውቃሉ? እያንዳንዱ አተም ውስጥ ከፍተኛ የኃይል ምንጭ ይገኛል። ኒውክሊየር ፊሽን በሚባል አተሞችን ለሁለት የመሰንጠቅ ሂደት አማካኝነት፤ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንደሚገኝ ሳይንቲስቶች በጥናት አረጋግጠዋል። ይህ የሙቀት ኃይል እንፋሎትን ሲፈጥር እንፋሎቱ ደግሞ በተራው ተርባይኖችን በማንቀሳቀስ ለከተሞችና እና ለሰፋፊ ኢንዱስትሪዎች የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይልን ያመነጫል። አንዲት ቅንጣት የምታህል የኒውክሊየር ነዳጅ ዩራኒየም በአስደናቂ ሁኔታ ግዙፍ የኃይል ምንጭን ታስገኛለች።
ለምሳሌ ያህል፤ አንዲት ትንሽዬ የጣታችንን ያህል መጠን ያላት የዩራኒየም ነዳጅ ዘንግ፤ አንድ ቶን ያህል የከሰል ድንጋይን ወይም ብዙ ሺህ ሊትር ነዳጅን የሚስተካከል የኤልክትሪክ ኃይልን ትሰጠናለች። ይህም ማለት የኒውክሊየር ሀይል ጥቂት የኒዩክሊየር ነዳጅን በመጠቀም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይልን ያመነጫል ማለት ነው።

የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ፤ ሳይቆራረጥ ቀንና ለሊት 24/7 አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን ይሰጠናል። የኒውክሊየር ኃይል እንደ ንፋስ፤ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ እና የፀሐይ ፓኔል የኃይል ምንጮች በአየር ንብረት ላይ ጥገኛ ሳይሆን፤የማያቋርጥ ኃይል በመስጠት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ቤቶች፤ ትምህርት ቤቶች ፤ የንግድ ስራዎች እና ኢንዱስትሪዎች ኃይል ይሰጠናል።
በተጨማሪም፥ ኒውክሊየር ሳይንስ በእለት እለት ህይወታችን ውስጥ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። በሆስፒታሎች ውስጥ ሀኪሞች በሽታን እንዲመረምሩና ህክምናቸውን እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል። ኤም አር አይ (MRI) እና የኒውክሊየር ህክምና ቅኝት ማድረጊያ፤የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ዶክተሮች በሰዎች አካላት ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድመው መለየት እንዲችሉ ያግዛቸዋል።
በሌላ ረገድ፣ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ በህዋ ምርምርና አሰሳ ውስጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። አንዳንድ የህዋ መንኮራኩሮች የራዲዮአይሶቶፕ ኃይል ማመንጫ ሥርዓት (RTG) በመጠቀም ኃይል ያመነጫሉ። ይህ ሥርዓት ከራዲዮአክቲቭ አይዞቶፖች በሚለቀቀው ሙቀት ኤሌክትሪክ በማመንጨት፣ የፀሐይ ብርሃን በቂ በማይሆንባቸው ሩቅ የህዋ አካባቢዎችም መንኮራኩሮች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሠሩ ያስችላል። በዚህም የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የህዋ ምርምርና አሰሳ ተልዕኮዎችን ለማሳካት ወሳኝ ድጋፍ ያደርጋል።
አሁንም ድረስ፤ ሳይንቲስቶችና የኒውክሊየር መሀንዲሶች፤ አዳዲስ ደህንነታቸው የተጠበቀ፤ ውጤታማና ይበልጥ አስተማማኝ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ላይ ይገኛሉ።
ለከተሞች ብርሃን ከመስጠት ጀምሮ፤ ዶክተሮች ህይወትን እንዲታደጉ ከማስቻል በዘለለ የህዋ ላይ አሰሳ ጉዞን እስከ መደገፍ ድረስ የላቀ ጠቀሜታ ያለው የኒውክሊየር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የአተም ኃይል አለማችንን እንዴት በብዙ መንገድ እያሻሻለ እንደመጣ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።
ኒውክሊየር ኃይል ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?


የኒውክሊየር ኃይል አስተማማኝና የማይለዋወጥ የኃይል ምንጭ በመሆኑ
የኒውክሊየር ኃይል አስተማማኝ፣ የማይለዋወጥና ለመሠረታዊ የኃይል ፍላጎት (Baseload) ተስማሚ የኤሌክትሪክ ምንጭ ነው። የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫዎች በአየር ሁኔታ ላይ ጥገኛ አይደሉም፤ ስለሆነም በቀንና በሌሊት በተከታታይ ሊሠሩ ይችላሉ። በተለምዶ እስከ 18 ወራት ያህል ያለማቋረጥ ከሠሩ በኋላ ለየት ላለ ጥገናና ለነዳጅ መሙላት ይቆማሉ።
ኒውክሊየር ኃይልን ወደ የኢትዮጵያ የኃይል አማራጭ (Energy Mix) ማካተት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማረጋጋት እና በረጅም ጊዜ ተጠቃሚዎች ለኤሌክትሪክ የሚያወጡትን ዋጋ ለመቀነስ ሊያግዝ ይችላል።

ንጹህና ለአካባቢ ተስማሚ በመሆኑ
በኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ውስጥ ኤሌክትሪክ በሚመነጭበት ወቅት ካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO₂) ወደ ግሪን ሀውስ ጋዝ በቀጥታ አይለቀቅም። ስለዚህ ኒዩክሊየር ኃይል የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና የንጹህ ኃይል ሽግግርን ለመደገፍ ጠቃሚ ሚና ይኖረዋል።

በረጅም ጊዜ ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ
የኒውክሊየር ኃይል ለረጅም ጊዜ ሊያገለግል የሚችል የተረጋገጠ የቴክኖሎጂ አማራጭ ሲሆን፣ የዩራኒየም ነዳጅን ይጠቀማል። የኒውክሊየር ማመንጫዎች የረጅም የሥራ ዕድሜ፣ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት እና ከነዳጅ አጠቃቀም አንጻር ከፍተኛ የኃይል ውጤታማነት ያላቸው በመሆናቸው፣ በረጅም ጊዜ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ወጪን በተመጣጣኝ ደረጃ ለማስቀመጥ ሊያግዙ ይችላሉ። ዘመናዊ የኒውክሊየር ማመንጫዎች የአገልግሎት ዕድሜያቸው እስከ 60 ዓመት ሊደርስ የሚችል ሲሆን፣ በተጨማሪም ለ20 ዓመታት ሁለት ጊዜ ሊራዘም ይችላል።

ለኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ዕድገት ያለው ሚና
የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ በአገልግሎትና በአቅርቦት ሰንሰለት በኩል ለሀገራዊና ለአካባቢያዊ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል። በማመንጫው ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችና ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራና የንግድ ዕድሎች በመፍጠር ኢኮኖሚን ያነቃቃል።
አስተማማኝና በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መኖሩም ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብና የኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን የሚያግዝ መሠረተ ልማት ይሆናል።

ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው ሚና
የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ በግንባታ ወቅት ብዙ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል፤ ይህም ከማመንጫው ግንባታ ጀምሮ በኋላም ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የሙያ ዕድሎችን ይፈጥራል። በተለይም በኢንጂነሪንግ፣ በኒውክሊየር ሳይንስ፣ በአይቲ፣ በኮንስትራክሽን ፣ በጥገና፣ በደህንነትና በማኔጅመንት ዘርፎች ከፍተኛ የእውቀትና የክህሎት የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ።
በመሆኑም የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም ከግንባታ እስከ ሥራ ማስኬድና ጥገና ድረስ በርካታ የሰው ኃይል ልማትና የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ለኢትዮጵያ የእውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ጉዞ | የነገዋን ሀገር በንጹሕ እና ታዳሽ ኃይል ወደ ብልጽግና የማሻገር ታሪካዊ ስትራቴጂ!
ክቡር ምክትል ኮሚሽነር አብዱረዛቅ ዑመር ከኢቢሲ ጋር በኢትዮጵያ የኒዩክሊየር ኃይል ልማት ዙሪያ ያደረጉት አጭር ቆይታ
ኢትዮጵያና ሩሲያ በሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል ልማት ትብብራቸውን ያጠናክራሉ

የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አብዱረዛቅ ኡመር በቅርቡ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ክቡር ኢቭጄኒ ቴሬክሂን ጋር በኢትዮጵያ የኒዩክሊየር ኃይል ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በመቀበል ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያን ሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ ግብር ለማፋጠን ሩሲያ ለምታሳየው የጋራ ራዕይና ቁርጠኝነት ጥልቅ ምስጋናውን እንደሚያቀርብ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።
ይህ ስትራቴጂካዊ ትብብር ጠንካራ የኒውክሊየር መሠረተ ልማት መገንባት፣ ከፍተኛ ደረጃ ያለው የሰው ኃይል ማፍራት፣ የኢንዱስትሪ ትብብርን ማስፋፋት እና የሕዝብ ግንዛቤ እና እምነትን ማጎልበት ላይ ያተኩራል።
ይህ የጋራ ትብብር ለኢትዮጵያ ንጹህ፣ ዘላቂና የማይለዋወጥ የኃይል ምንጭን እውን በማድረግ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስፈላጊ የለውጥ ምዕራፍ እንደሚሆን በውይይቱ ተነስቷል።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ 70ኛ አጠቃላይ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ 181 አባል ሀገራት አባል የሆኑበት የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) በዚህ ሳምንት በኦስትሪያ ቪየና በመገኘት 70ኛውን አጠቃላይ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል። ጉባኤው ሰፊ የውይይት መርሐ ግብርን ያካተተ ሲሆን፣ በካንሰር ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ፎረም፣ የጎንዮሽ ዝግጅቶች፣ አውደ ርዕዮች እና ጉብኝቶችን ያካሂዳል።


የጉባኤው የመክፈቻ ስብሰባ ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ራፋኤል ግሮሲ ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎችና ያስመዘገባቸውን በጎ ተጽእኖዎች አቅርበዋል።
በጉባኤው ወቅት ተወካዮች ከኒውክሊየር ደህንነትና ጥበቃ፣ ከIAEA ሴፍጋርድ (Safeguards) እንዲሁም ከኒውክሊየር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ትግበራ ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎችን፣ የቴክኒክ ትብብርን ጨምሮ፣ ለማጠናከር በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ተወካዮቹ ፥የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) የ2025 ዓመታዊ ሪፖርት፣ የ2027 የበጀት ማሻሻያ እና የኤጀንሲውን የ2025 የፋይናንስ ሪፖርቶች ይመለከታሉ። ይህም ለ2027 የቴክኒክ ትብብር ፈንድ የሚደረጉ መዋጮዎችን ያካትታል። በተጨማሪም የIAEA የአስተዳደር ቦርድ (Board of Governors) አባላት በጉባኤው ወቅት ይመረጣሉ።
ክቡር አምባሳደር ኃይለሥላሴ ሱባ፣ በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ ሚሲዮን እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካይ፣ እንዲሁም ሁለተኛ ጸሐፊ ወ/ሮ ቤተልሔም መኮንን፣ የኢትዮጵያን ቡድን በመምራት በ70ኛው የIAEA አጠቃላይ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
