የኒውክሊየር ኃይል በአካባቢያችን ያሉ ነገሮች ከሚሰሩበት ከጥቃቅን አተሞች እንደሚገኝ ያውቃሉ? እያንዳንዱ አተም ውስጥ ከፍተኛ የኃይል ምንጭ ይገኛል። ኒውክሊየር ፊሽን በሚባል አተሞችን ለሁለት የመሰንጠቅ ሂደት አማካኝነት፤ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንደሚገኝ ሳይንቲስቶች በጥናት አረጋግጠዋል። ይህ የሙቀት ኃይል እንፋሎትን ሲፈጥር እንፋሎቱ ደግሞ በተራው ተርባይኖችን በማንቀሳቀስ ለከተሞችና እና ለሰፋፊ ኢንዱስትሪዎች የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይልን ያመነጫል። አንዲት ቅንጣት የምታህል የኒውክሊየር ነዳጅ ዩራኒየም በአስደናቂ ሁኔታ ግዙፍ የኃይል ምንጭን ታስገኛለች።

ለምሳሌ ያህል፤ አንዲት ትንሽዬ የጣታችንን ያህል መጠን ያላት የዩራኒየም ነዳጅ ዘንግ፤ አንድ ቶን ያህል የከሰል ድንጋይን ወይም ብዙ ሺህ ሊትር ነዳጅን የሚስተካከል የኤልክትሪክ ኃይልን ትሰጠናለች። ይህም ማለት የኒውክሊየር ሀይል ጥቂት የኒዩክሊየር ነዳጅን በመጠቀም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይልን ያመነጫል ማለት ነው።

የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ፤ ሳይቆራረጥ ቀንና ለሊት 24/7 አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን ይሰጠናል። የኒውክሊየር ኃይል እንደ ንፋስ፤ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ እና የፀሐይ ፓኔል የኃይል ምንጮች በአየር ንብረት ላይ ጥገኛ ሳይሆን፤የማያቋርጥ ኃይል በመስጠት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ቤቶች፤ ትምህርት ቤቶች ፤ የንግድ ስራዎች እና ኢንዱስትሪዎች ኃይል ይሰጠናል።

በተጨማሪም፥ ኒውክሊየር ሳይንስ በእለት እለት ህይወታችን ውስጥ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። በሆስፒታሎች ውስጥ ሀኪሞች በሽታን እንዲመረምሩና ህክምናቸውን እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል። ኤም አር አይ (MRI) እና የኒውክሊየር ህክምና ቅኝት ማድረጊያ፤የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ዶክተሮች በሰዎች አካላት ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድመው መለየት እንዲችሉ ያግዛቸዋል።

በሌላ ረገድ፣ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ በህዋ ምርምርና አሰሳ ውስጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። አንዳንድ የህዋ መንኮራኩሮች የራዲዮአይሶቶፕ ኃይል ማመንጫ ሥርዓት (RTG) በመጠቀም ኃይል ያመነጫሉ። ይህ ሥርዓት ከራዲዮአክቲቭ አይዞቶፖች በሚለቀቀው ሙቀት ኤሌክትሪክ በማመንጨት፣ የፀሐይ ብርሃን በቂ በማይሆንባቸው ሩቅ የህዋ አካባቢዎችም መንኮራኩሮች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሠሩ ያስችላል። በዚህም የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የህዋ ምርምርና አሰሳ ተልዕኮዎችን ለማሳካት ወሳኝ ድጋፍ ያደርጋል።

አሁንም ድረስ፤ ሳይንቲስቶችና የኒውክሊየር መሀንዲሶች፤ አዳዲስ ደህንነታቸው የተጠበቀ፤ ውጤታማና ይበልጥ አስተማማኝ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ላይ ይገኛሉ።

ለከተሞች ብርሃን ከመስጠት ጀምሮ፤ ዶክተሮች ህይወትን እንዲታደጉ ከማስቻል በዘለለ የህዋ ላይ አሰሳ ጉዞን እስከ መደገፍ ድረስ የላቀ ጠቀሜታ ያለው የኒውክሊየር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የአተም ኃይል አለማችንን እንዴት በብዙ መንገድ እያሻሻለ እንደመጣ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።