ኢትዮጵያን ጨምሮ 181 አባል ሀገራት አባል የሆኑበት የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) በዚህ ሳምንት በኦስትሪያ ቪየና በመገኘት 70ኛውን አጠቃላይ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል። ጉባኤው ሰፊ የውይይት መርሐ ግብርን ያካተተ ሲሆን፣ በካንሰር ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ፎረም፣ የጎንዮሽ ዝግጅቶች፣ አውደ ርዕዮች እና ጉብኝቶችን ያካሂዳል።


የጉባኤው የመክፈቻ ስብሰባ ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ራፋኤል ግሮሲ ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎችና ያስመዘገባቸውን በጎ ተጽእኖዎች አቅርበዋል።
በጉባኤው ወቅት ተወካዮች ከኒውክሊየር ደህንነትና ጥበቃ፣ ከIAEA ሴፍጋርድ (Safeguards) እንዲሁም ከኒውክሊየር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ትግበራ ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎችን፣ የቴክኒክ ትብብርን ጨምሮ፣ ለማጠናከር በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ተወካዮቹ ፥የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) የ2025 ዓመታዊ ሪፖርት፣ የ2027 የበጀት ማሻሻያ እና የኤጀንሲውን የ2025 የፋይናንስ ሪፖርቶች ይመለከታሉ። ይህም ለ2027 የቴክኒክ ትብብር ፈንድ የሚደረጉ መዋጮዎችን ያካትታል። በተጨማሪም የIAEA የአስተዳደር ቦርድ (Board of Governors) አባላት በጉባኤው ወቅት ይመረጣሉ።
ክቡር አምባሳደር ኃይለሥላሴ ሱባ፣ በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ ሚሲዮን እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካይ፣ እንዲሁም ሁለተኛ ጸሐፊ ወ/ሮ ቤተልሔም መኮንን፣ የኢትዮጵያን ቡድን በመምራት በ70ኛው የIAEA አጠቃላይ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
