ኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይልን ለማልማት በሚያስፈልጉ የፋይናንስ ማዕቀፎችና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ላይ ያተኮረ ክልላዊ ስልጠና ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ማካሄድ ጀምራለች ።

የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ስልጠና፣ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ-ግብር ለመጀመር በዝግጅት ላይ ላሉ ሀገራት የፋይናንስ ማዕቀፎችን ለመረዳትና ተግባራዊ አቅምን ለማጎልበት ያለመ ነው።

የኒውክሊየር ኃይል መርሃ-ግብርን ለማቋቋም ከፍተኛ የመነሻ ካፒታል፣ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ እቅድና የተለያዩ የገንዘብ ምንጮችን ማስተባበር የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ የፋይናንስ ማዕቀፎችን በትክክል መንደፍ ለመርሃ-ግብሩ ስኬታማነት ወሳኝ ነው።
ከ22 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 39 ተወካዮችን ያሰባሰበው ይህ አውደ ጥናት በአህጉሪቱ ንጹህ እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት እንዲሁም ዘላቂ የኃይል ልማትን ለማፋጠን የተደረገ ትልቅ እርምጃ ነው። ስልጠናው “ለኒውክሊየር ኃይል መርሃ-ግብሮች ጀማሪ ሀገራት የፋይናንስ ማዕቀፎች” በሚል ርዕስ እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።